Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ በዓለም ፊት በራሷ አቅም ለውጥ የማምጣት አቅም ይዛ መቅረብ አለባት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፍሪካ በዓለም ፊት ተደራዳሪ አካል ሳትሆን በራሷ አቅም ለውጥ የማምጣት አቅም ይዛ መቅረብ አለባት አሉ፡፡
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ‘ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማሳለጥ፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ’ በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኬንያ መንግስት የመጀመሪያውን ጉባኤ ባለፈው ዓመት ባስተናገደበት ወቅት በርካታ ፈር ቀዳጅ ተግባራት እንዲጀመሩ በማድረጉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የቴክኖሎጂ፣ የጊዜ እና የፋይናንስ ተግዳሮቶችን ለመቀልበስ ባለን አቅም በራሳችን ጥረት አሁን መጀመር አለብን ብለዋል።
አፍሪካ አህጉሪቱን እና ዓለምን መመገብ የሚችል ጥቅም ላይ ያልዋለ ለም የእርሻ መሬት መገኛ፣ የበርካታ ታዳሽ ኃይል ምንጭ ምድር መሆኗን ጠቅሰዋል።
እኛ አፍሪካውያን እዚህ የተሰባሰብነው በአየር ንብረት ጉዳይ ስለ ህልውናችን ለመደራደር ሳይሆን በራሳችን አቅም ለአየር ንብረት ተፅዕኖ ምላሽ ለመሥጠት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከሰባት ዓመታት በፊት በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር አማካኝነት እስካሁን ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ራስን ከመቻል አልፎ ወደ ውጭ ለመላክ ያስቻላትን ውጤት ማስመዝገቧን አብራርተዋል፡፡
የምግብ ስርዓትን በተመለከተ አፍሪካ ራሷን ከመመገብ አልፋ ባላት ፀጋ ወደ ተቀረው ዓለም የመላክ አቅም እንዳላት ጠቅሰው፤ ይህን እውን ለማድረግ ተገቢውን ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ በዓለም ፊት ተደራዳሪ አካል ሳትሆን በራሷ አቅም ለውጥ የማምጣት አቅም ይዛ መቅረብ እንዳለባት ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ያለነው ትውልዶች የታለሙ ግቦችን በማሳካት የመጀመሪያዎቹ የመሆን እድል አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን ማድረግ ካቃተን በታሪክ የመጀመሪያው ተወቃሽ እንሆናለን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ በፈረንጆቹ 2027 ለማስተናገድ እጩ በመሆኗ መላው ዓለም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ጉባኤውን እንዲታደም ከወዲሁ ጋብዘዋል።
በመሳፍንት ብርሌ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.