በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎች የአፍሪካ ሃሳብ በአንድ ድምጽ እንዲሰማ የሚያስችሉ ናቸው
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎች የአህጉሪቱ ሃሳብ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በአንድ ድምጽ እንዲሰማ የሚያስችሉ ናቸው አሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)።
2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ‘ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማሳለጥ፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ’ በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ሚንስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በጉባኤው ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ብቻ ሳይሆን ቀጣዮቹን አስርት አመታት የአፍሪካ እውነተኛ የእድገት ጊዜ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ይደረጋል።
ጉባኤው አፍሪካዊ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ በማፈላለግና ፋይናንስ፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ የሰው ኃይል ካፒታልና የፈጠራ ስነምህዳርን ለጋራ ብልጽግና በማንቀሳቀስ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ጉባዔውን እንድታዘጋጅ መወሰኑን ተከትሎ ባለሙያዎችን በማሰማራት ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል፡፡
በጉባዔው የሚነሱትን ሀሳቦችና ዝርዝር አጀንዳዎችን ለማዘጋጀት ከፖሊሲ አውጪዎች፣ ወጣቶችና የማህበረሰብ መሪዎች ጋር ሰፊ ምክክር ተደርጓልም ነው ያሉት።
መድረኩ ከሀሳብ ወደ ተግባር ሽግግር የሚደረግበት እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትሯ፥ በዛሬው ዕለትም ተፈጥሯዊ በሆኑ መፍትሔዎች፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ፣ በታዳሽ ኃይልና በዘላቂ መሰረተ ልማት ላይ በትኩረት ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የቅድመ ማስጠንቀቂያና ጤናን ጨምሮ በአየር ንብረት መላመድና ማገገም ዙሪያ የሚደረጉ ትብብሮች የ2ኛው ቀን አጀንዳ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በጉባኤው የ3ኛ ቀን ውሎ አፍሪካ መር የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔዎችን ወደ ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት መለወጥ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ውይይት ይደረጋል ነው ያሉት።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በፍጥነት እያደገች ባለችው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ አስደናቂ ስፍራዎች እንደሚጎበኙም ነው ሚንስትሯ የተናገሩት።
በዮናስ ጌትነት