የታላቁ ኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ምረቃ የዋዜማ ዝግጅት በጉባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2017 (ኤፍ ኤምሲ) የኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊነት መገለጫ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ምረቃ የዋዜማ ዝግጅት በጉባ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተካሄደ ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተገኝተዋል፡፡
በተጨማሪም በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የቀድሞ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ሚኒስትሮች ታድመዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት የነበረው ታላቁ ኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ በርካታ ውስብስብ ሒደቶችን አልፎ በነገው ዕለት በይፋ ይመረቃል፡፡
የኢትዮጵያውያን ሕብረት እና አንድነት ውጤት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ምረቃ ሥነ ሥርዓትም በተለያዩ ሁነቶች በድምቅት የሚከበር ይሆናል፡፡
የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን አስመልክቶም በዛሬው ዕለት የዋዜማ ዝግጅት መርሐ ግብር በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በኅዳሴ ግድብ ግራና ቀኝ በተገነባውና 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው መንገድ የእግር ጉዞ አድርገዋል፡፡
አሁን ላይ የዋዜማ መርሐ ግብሩ በድሮን ትርዒትና በሌሎች ሁነቶች ነው በድምቀት እየተከበረ የሚገኘው፡፡
በመላኩ ገድፍ