ለቅርብና ሩቅ ጠላቶች ኢትዮጵያውያን የማይሞት ስም እንጂ የማይሞት አካል የለንም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብልጽግና የማይሳካ ለሚመስላቸው የቅርብና ሩቅ ጠላቶች እኛ ኢትዮጵያውያን የማይሞት ስም እንጂ የማይሞት አካል የለንም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ዳግማዊ ዓድዋና ኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊነት መገለጫ የሆነው ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ የምረቃ ሥነ ሥርዓት በጉባ እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት የኢትዮጵያን ስኬት ለሚያደናቅፉ የቅርብና ሩቅ ጠላቶች ባስተላለፉት መልዕክት ÷ እኛ ኢትዮጵያውያን የማይሞት ስም እንጂ የማይሞት አካል የለንም ብለዋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን አካላችን ሞቶ የማይሞት ስም ለማስቀረት የማይሞት አሻራ ለማኖር የምንተጋ ሕዝቦች ነን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ስለሆነም ከእኛ ጋር መጋጨት ሳይሆን መስማማት ብቻ ነው የሚያዋጣው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ምክንያቱም ለሺህ ዘመናት የሞከሩን አንዴም አልተሳካላቸውም ብለዋል፡፡
ከእንግዲህ በኋላ የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን በመሆኑ ኢትዮጵያ ዳግም ዓድዋን ለጥቁር ሕዝቦች ደጋግማ ማሳየቷ አይቀሬ ነው ፤መላው የጥቁር ሕዝብም ለመበልጸግ በትብብር እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ኢትዮጵያን አከብረው ለተገኙ እንግዶችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ