Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ሕዳሴ ግድብ በመመረቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለምረቃ በመብቃቱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ያስተላለፈው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የዘመናት ቁጭት ማብቂያ የትውልዱ የድል ሐውልት ለመሆን የበቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአሏህ ፈቃድ በኢትዮጵያውያን የተባባረ ክንድ እውን ለመሆን በቅቷልና ደስታችን ከፍ ያለ ነው።
ህዝባችን ከሌለው ላይ ቀንሶ፣ የኑሮ ደረጃ፣ የገቢ ሁኔታ ሳይገድበው፣ ድህነትን ታሪክ በማድረግ ቁጭት፣ ሀብቱ እያለ ከብርሃን የራቀበትን ዘመን ለማካካስ፣ የቻለውን ሁሉ አድርጎ እንደ አይን ብሌኑ የጠበቀው ግድብ ዛሬ ለምርቃት በመብቃቱ እጅግ ያስደስታል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወንድም የተፋሰሱ ሀገራት ሕዝቦች ሳይጎዱ ሀብታችንን በአግባቡ መጠቀም የመፈላጋችን ውጥን እንጅ ሌላ አይደለም። ማንም ማንንም ሳይጎዳ የውሃ ሃብታችንን በጋራ መጠቀም እንችላለን፣ ሕዳሴም ይህንኑ አሳይቷል። በብርሃን እጦት ሲሰቃይ ለኖርነው እኛ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው።
ይህ ደማቅ ታሪክ እንዲፃፍ የላብ፣ የደም፣ የሕይወት ዋጋ የከፈሉ ሁሉ ክብር ይገባቸዋል። በዲፕሎማሲው አውድ ኢትዮጵያ መቼም የውሃ ሃብቷን መጠቀም የማያስችላትን አሳሪ ስምምነት እንድትፈርም፣ ሕዳሴም ተጠናቅቆ ለዛሬ ድል እንዳይበቃ ሲተጉ የነበሩ አካላትን በቋንቋቸው ጭምር ፊት ለፊት እየተጋፈጡ፣ እውነቱን ላስረዱም ሁሉ ትልቅ ምስጋና እና ክብር አለን።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ የመተባበራችን ውጤት የድላችን ማብሰሪያ የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከብዙ መስዋእትነት እና ፈታኝ ጉዞ በኋላ ለዚህ በመብቃቱ የተሰማውን ደስታ ይገልፃል።
ሀብታችንን በመጠቀም ቀጥሎ ለምንፈልጋቸው ተመሳሳይ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በጋራ እንድንቆምም ጥሪውን ያቀርባል። ህዝበ ሙስሊሙ እስከፍፃሜው ያሳየውን ቁርጠኛነት የታየበት አበርክቶም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያረጋግጣል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት
ጳጉሜን 4፣ 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.