የሀላባ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በፊፋ ምዘና ተደረገለት
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀላባ ዓለም አቀፍ ስታዲየም መጫወቻ ሜዳ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ባለሙያ ምዘና ተደርጎለታል፡፡
ምዘናውን ያከናወነው የፊፋ ባለሙያ እንግሊዛዊው ኮሊን መጫወቻ ሜዳው ጨዋታ ለማከናወን ብቁ መሆኑን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጿል።
ሜዳው ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ እንደተሰራ በመግለፅ የትኛውንም አይነት ጨዋታ የማከናወን አቅም እንዳለው በምርመራችን አረጋግጠናል ነው ያለው፡፡
የፊፋን አሰራር ጠብቆ መጫወቻ ሜዳው ፈቃድ ሲያገኝ ከድሬዳዋ ቀጥሎ በሀገራችን ሁለተኛው የፊፋ ፈቃድ ያለው የአርቴፊሻል ሜዳ ይሆናል።
ግንባታውን ያከናወነው የታን ኢንጂነሪንግ ባለቤት ፎዓድ ኢብራሂም በሀገራችን ያለውን የመጫወቻ ሜዳ እጥረት ለመቅረፍ እንሰራለን ብለዋል፡፡
በቅርቡ በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ አርቴፊሻል መጫወቻ ሜዳ ገንብተን እናጠናቅቃለን ሲልም ጠቁሟል።
ሙሉ በሙሉ ከህዝብ በሚሰበሰብ ገንዘብ እየተሰራ ያለው የሀላባ ስታዲየም ሙሉ ግንባታውን ለማጠናቀቅ አስቀድሞ በወጣ ግምት 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ይፈጃል ተብሏል።
በሰለሞን በቀለ