Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች 2018 አዲስ ዓመትን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በመልዕክታቸው፤ በለውጡ ዓመታት ተግዳሮቶችን በመቋቋም ግብርና፣ ኮሪደር ልማት፣ ቱሪዝም እና ዲፕሎማሲን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የኢትዮጵያን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

የጽናት እና የአመራር ብቃት ማሳያ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን ሽግግር የተደረገበት መሆኑን ገልጸው፤ በአዲሱ ዓመት ለላቀ ስኬት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳዳር ሙስጠፋ መሐመድ በበኩላቸው፤ የ2018 ዓ.ም ጅማሮ በከፍተኛ ብሥራት እና ድል የታጀበ ነው ብለዋል።

በግድቡ ላይ እንደ አንድ ሆነን ያሳረፍነውን አሻራ በቀጣይ በግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ መድገም አለብን በማለት ገልጸው፤ በአዲሱ ዓመት ብስራት እና ድሎቻችን ይበልጥ የሚያንጸባርቁበት እንዲሆን እመኛለሁ ነው ያሉት።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)፤ ያለፈው ዓመት የድል ጉዞን በማስቀጠል ለአዲስ የብልጽግና ምዕራፍ በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አዲሱን ዓመት ስንቀበል የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳትና ማዕዳችንን በማጋራት አንድነታችንን ይበልጥ ልናጠናክር ይገባል ብለዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ 2017 ዓ.ም ለክልላችንና ለሀገራችን የለውጥ፣ የትግልና የድል ዓመት ነበር ሲሉ አስታውሰው፤ በጋራ ጥረት እና ጽናት ፈተናዎችን በመሻገር ተስፋ ሰጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

2018 ዓ.ም የትናንትናውን ድል በመገንባት፣ የነገውን ብሩህ ተስፋ እውን በማድረግ ህዝቡን ከድህነት የማውጣት ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፤ በአዲሱ ዓመት የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እንዲሁም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ሊያሻግሩ የሚችሉ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

የሕዳሴ ግድብ መመረቁ ትልቅ ብስራት መሆኑን አንስተው፤ የግድቡ ተሞክሮ ኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምራ ማጠናቀቅ እንደምትችል ማሳየቱን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.