አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አፈ ጉባኤው በመልዕክታቸው፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ተከትሎ በታላቅ ርዕይና የይቻላል መንፈስ በሀገራችን የተገነቡ፣ እየተገነቡ ያሉና የሚገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሀገራዊ ከፍታ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
እስካሁን እጅግ አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል ያሉት አፈ ጉባኤው፤ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ አኳያ በግብርና ምርታማነት ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በሌማት ትሩፋት ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ በቢሊየን የሚቆጠር ችግኝ በመትከል ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ጤናማ አካባቢን በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።
በከተሞች ምቹና ፅዱ የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር የተቻለበት የኮሪደር ልማት ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፤ በከተሞች እየተካሄደ ያለው ልማት እጅግ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአይቻልም መንፈስን የሰበረ፣ የአፍሪካ ተምሳሌት እና የሀገራችን የብልፅግና መዳረሻ ማሳያ ነው ብለዋል።
እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ከውጭና ከውስጥ ያሉ በርካታ ፈተናዎችን በመስዋዕትነት፣ በፅናትና በትዕግስት በመሻገር እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመሥራት ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በግብርና፣ በወጪ ንግድ፣ በቱሪዝም ዕመርታ አሳይታለች ብለዋል።
እነዚህ ውጤቶች የሀገራችንን ማንሰራራት የሚያሳዩ እና የነገዋን የበለፀገች ኢትዮጵያ ከወዲሁ የሚያመላክቱ ተስፋዎች በመሆናቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ከፍታ አይቀሬ ነው ሲሉ ገልጸዋል።