Fana: At a Speed of Life!

የሕዳሴ ግድብ መመረቅ የጋራ ስኬትን ከማሳየቱ ባለፈ የኢትዮጵያን የማንሠራራት ጊዜ ያረጋገጠ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለምረቃ መብቃቱ የኢትዮጵያውያንን የጋራ ስኬት ከማሳየቱ ባለፈ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጊዜ ያረጋገጠ ነው አሉ ምሁራን።

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ሙሉነህ ለማ (ዶ/ር) ÷ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽናት፣ አንድነት እና አይበገሬነት መገለጫ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም ልዩነት ገንዘባቸውን፣ ሃብታቸውን እና እውቀታቸውን ለሕዳሴ ግድብ ማዋጣታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምሕንድስና ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር በረከት ነፃነት በበኩላቸው ፥ የሕዳሴ ግድብን በስኬት ማጠናቀቅ መቻል በቀጣይ መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በር የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡

በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሒደት ከፍተኛ የእውቀት ሽግግር እና የልምድ ልውውጥ በመገኘቱ ለሌሎች ሥራዎች በተሞክሮነት እንደሚወሰድ ጠቅሰዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ብርሃን በመስጠት የቀጣናውን ትስስር እንደሚያሳልጥም ነው ያብራሩት፡፡

ዳግማዊ ዓድዋ የሆነው ሕዳሴ ግድብ የተሳሰረ ልማትና የጋራ እድገትን ያመጣል ያሉት ደግሞ በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ መምህርና ተመራማሪ ከድር እስማኤል ናቸው፡፡

የሕዳሴ ግድብ ከብርሃን ምንጭነት ባሻገር በራስ አቅም መሥራት መቻልን፣ ጫና መቋቋምን እና የሕዝብ አንድነትን ያሳየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ምሁራኑ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በርካታ ውስብስብ ችግሮችን አልፎ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአስጨናቂ ጉዱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.