የኢትዮጵያና ኩባን ዘርፈ ብዙ ትብብር ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ኩባ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በኩባ ሕዝቦች ወዳጅነት ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንትና የሀገሪቱ ፓርላማ አባል ፈርዲናንድ ጎንዛሌስ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱም የኩባ ልዑካን ቡድን አባላት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለምረቃ በመብቃቱ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነት ማሳያ ነው ያሉት ልዑካኑ÷ በሀገሪቱ የተጀመረውን የብልጽግ ጉዞ ማፋጠን እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡
ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የሕዳሴ ግድብ በራስ አቅም መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማከናወን እንደሚቻል ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ትምህርት የሰጠ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በምክክሩ ወቅት ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያና ኩባ ለረጅም ዓመታት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አውስተው÷ በቀጣይ የፓርቲ ለፓርቲ፣ የመንግስት ለመንግስትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ግንኙነት በመግባቢያ ስምምነትና ሌሎች መንገዶች ተቋማዊ ለማድረግና ለመተግበር የሀገራቱ ገዢ ፓርቲዎች ቀዳሚውን ሚና እንዲወጡ ተስማምተዋል፡፡
በመንግስት በኩል ሁለቱ ወገኖች የቆዩ የትብብር መስኮችን በማጠናከርና አዳዲስ እድሎችን በማስፋት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በሀገራቱ እና በገዢ ፓርቲዎቹ መካከል ያለውን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ልዑካኑ ከኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ቡድን አባላት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ እና ኩባ መካከል ባለው የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር የፓርላማ ወዳጅነት እንዲሁም የፓርቲ ግንኙነት ላይ ተወያይተዋል፡
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ሊቀ መንበር አብዱልቃድር ገልገሎ (ዶ/ር) ÷ ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከርና ለማስፋት ባላት ቁርጠኝነት አዳዲስ ትብብርን ለመፍጠር በትኩረት ትሰራለች ብለዋል።
ፈርዲናንድ ጎንዛሌስ በበኩላቸው ÷ ሀገራቱ ባላቸው መልካም ግንኙነትና ዘላቂ አጋርነት አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነው ÷ ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡