Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና የማለፍ ምጣኔን ማሳደግ ተችሏል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በተሰራ ስራ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና የማለፍ ምጣኔን ማሳደግ ተችሏል አለ የክልሉ ትምህርት ቢሮ፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የቢሮው ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንደገለጹት፥የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ውጤትን ለማሻሻል በተሰራው ስራ የተሻለ ውጤት ተገኝቷል፡፡

በክልሉ የ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 33ሺህ 782 ተማሪዎች ውስጥ 5 ነጥብ 7 በመቶ ያህሉ 50 በመቶና ከዚያ በላይ ውጤት በማምጣት ማለፋቸውን ተናግረዋል፡፡

በ2016 የትምህርት ዘመን በክልሉ ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ 3 ነጥብ 4 በመቶ ያህሉ ማለፋቸውን አስታውሰው፥ በ2017 የትምህርት ዘመን ያለፉ ተማሪዎች ምጣኔ ካለፈው ጋር ሲነጻጸር 67 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን አመልክተዋል፡፡

በክልሉ በአጠቃላይ በ12ኛ ክፍል ውጤት በርካታ ማሻሻያ ታይቷል ያሉት ኃላፊው፥ በክልሉ የሚገኙ አራት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ ማሳለፋቸውን ጠቅሰዋል።

የትምህርት ጥራትና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በተሰራው ስራ የተሻለ ውጤት መምጣቱን ገልጸው፥ ይህን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በብርሃኑ በጋሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.