ለሕዳሴ ግድብ ያሳየነውን አንድነት ሀገራዊ መግባባትን ለማጽናት ልንጠቀምበት ይገባል – አቶ ኡስማን ሱሩር
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያሳየነውን አንድነትና ጽናት ሀገራዊ መግባባትን ለማጽናት ልንጠቀምበት ይገባል አሉ በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር።
የሕዳሴ ግድብ መመረቁን አስመልክቶ በዱራሜ ከተማ በተካሄደው የደስታ መግለጫ ሰልፍ ላይ የተገኙት አቶ ኡስማን ÷ በግድቡ የተባበርነውን ለቀጣይ ብልጽግና በመትጋት በግብርና፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፉ ላይ መድገም ይገባል ብለዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ በጋራ ክንዳችን፣ በኢትዮጵያውያን አንድነትና ቁርጠኝነት የገነባነው የትውልድ ዐሻራ፣ የኢትዮጵያዊነት መለያ ምልክት፤ የኩራታችን ምንጭ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ግድቡ በሕብረት የማሸነፍ ማሳያና ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑን አውስተው ÷ የኢትዮጵያዊያን የሕብረ ብሄራዊ አንድነታችን መለያ ምልክት እንደሆነም አመላክተዋል።
ግድቡ ከድህነት አዙሪት ለመውጣት የቁርጠኝነት ማሳያ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ኡስማን÷ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሔሩ፣ ሃይማኖቱና የኑሮ ደረጃው ሳይለየው በአንድነት ተሳስሮ አርማውን ከፍ ያደረገበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ግድቡ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሮ ምልክት፣ የይቻላል መንፈስ እርሾ እንዲሁም የቁጭት ታሪካችን ማብሰሪያ ነው ብለዋል፡፡
የግድቡ መጠናቀቅ በራስ አቅም መቆም ለሚሹ የአፍሪካ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የተስፋ ችቦ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
የዛሬው ድላችን ለቀጣይ ልማቶችና የጋራ ጉዳዮች የመተማመንና የመደጋገፍ መሰረት ይጥላል ያሉት አቶ ኡስማን÷ ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ ላበረከተው የክልሉ ሕዝብ ምስጋና አቅርበዋል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!