በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊ ሀብቶችን ለመንከባከብ በትኩረት ይሰራል – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ታሪካዊ ሀብቶችን ለመንከባከብ በትኩረት ይሰራል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፡፡
የዎላይታ ህዝብ ዘመን መለወጫ ጊፋታ በዓል በሶዶ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ክልሉ ጊፋታን ጨምሮ የበርካታ ባህላዊ ክብረ በዓላትና ባህሎች መገኛ እንደመሆኑ ለህዝቦች አንድነት የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ መቻቻልና መተጋገዝ፣ አንድነትና ህብረት በጊፋታ በዓል መታየቱን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ እነኚህ ክብረ በዓላት ህዝቡ ለልማትና አንድነት ያለውን መተባበርና ህብረት ይበልጥ የሚያጠናክሩ መሆን እንዳለባቸው አስገነዝበዋል፡፡
ክልሉ ከተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘርፈ ብዙ የልማት ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸው፥ በተለይም ሰላሙን በመጠበቅ ያሉ ጸጋዎችን ለመጠቀምና ለሀገራዊ ማንሰራራት የሚጠበቅበትን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የጊፋታ በዓልን በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ለማዝመዝገብ ሂደት ላይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በጥላሁን ሁሴን እና አበበች ኬሻሞ