የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ምልክት ነው – አቶ አወል አርባ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ምልክትና የባህር በር የመስፈንጠሪያ ምስጢር ነው አሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፡፡
በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በማስመልከት የድጋፍና የደስታ መግለጫ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት ባስተላፉት መልዕክት፥ ግድቡ የዘመናት ልፋትና ቁጭት ውጤት መሆኑን ገልጸው፥ በኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የአይበገሬነት እና የይቻላል መንፈስ የተገነባ ነው ብለዋል፡፡
ለኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ምላሽ ከመስጠት ባሻገር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌትና የጋራ ብሔራዊ ትርክት መገንቢያ መሳሪያ መሆኑን አውስተዋል።
ከግድቡ ስኬት በኋላ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ቀጣይ ትኩረት መሆኑን ጠቁመው፥ ቀይ ባህርን መልሶ ማግኘት ያለውን ኢኮኖሚያዊና ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ አስረድተዋል፡፡