በኦሮሚያ ክልል ከ26 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ለአርሶ አደሮች ተከፋፈለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከ26 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ለአርሶ አደሮች በዛሬው ዕለት ተከፋፍሏል፡፡
በመርሐ ግብሩ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
አቶ አዲሱ አረጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የግብርና ዘርፉን ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር በትኩረት ይሰራል፡፡
በቢሾፍቱ ከተማ ለአርሶ አደሮች መከፋፈል የጀመሩት የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ለበጋ መስኖ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮች የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን ለተገቢው አላማ በማዋል ምርታማነታቸውን ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ግብር ቢሮ ም/ሃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ በበኩላቸው ÷ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች እንደሚሰራጩ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
ይህም በበጋ መስኖ በክልሉ ለማልማት የታቀደውን ሥራ በስኬት ለማጠናቀቅ እንደሚያስችል ነው ያብራሩት፡፡