ኢትዮጵያ በመድኃኒት ቁጥጥር የዓለም ጤና ድርጅትን 3ኛ ደረጃ የብቃት ማረጋገጫ አገኘች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በመድኃኒት ቁጥጥር የዓለም ጤና ድርጅትን 3ኛ ደረጃ (ማቹሪቲ ሌቭል-3) የብቃት ማረጋገጫ አገኘች፡፡
ድርጅቱ የሀገራት የህክምና ምርቶች ተቆጣጣሪ አካላት የቁጥጥር ስርዓት የደረሰበትን ደረጃ በመገምገም ደረጃ የሚሰጥ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ያገኘችው 3ኛ ደረጃ የተረጋጋና የተቀናጀ የቁጥጥር ሥርዓት ላይ መድረሷን ያመለክታል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መድኃኒቶች ጥራት፣ ደህንነትና ውጤታማነት በዓለም አቀፍ ደረጃ መረጋገጡን አመላካች ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር መሀመድ ያኩብ ጃናቢ፥ ኢትዮጵያ በዘርፉ የደረሰችበት ስኬት ለአህጉሪቱም ጭምር ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡
ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ይህንን ደረጃ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን እንዲሁም ሌሎች አጋር አካላት ምስጋና አቅርቧል።
የህብረተሰባችንን ጤና ለመጠበቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ስርዓት ለመፍጠር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡