ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት መሪነቷን ታጠናክራለች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ ትቀጥላለች አለ።
የባዮዲጂታል ቴክኖሎጂን በምግብና ግብርና ዘርፍ መጠቀም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ አህጉራዊ መድረክ ከ30 በላይ ሀገራት የተውጣጡ የዘርፉ ባለድርዎች እና የአጋር ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት ይካሄዳል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በመድረኩ እንዳሉት፥ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ወሳኝ ሚና አለው።
በዓለማችን ሊታረስ እየቻለ ካልታረሰ መሬት ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው በአፍሪካ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ ነገር ግን አሁንም ድረስ የምግብ ፍጆታ ከውጭ እንደሚገባ አንስተዋል።
አፍሪካ በተፈጥሮ የታደለችውን ለም መሬት በአግባቡ በማልማት አህጉሪቱን ከምግብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እንደምትወጣም አረጋግጠዋል።
በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ‘የአዲስ አበባ ስምምነት’ መጽደቁን አስታውሰዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ሀገር በቀል መፍትሄን የሚያመላክተው ስምምነት እንዲጸድቅ ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና እንደነበራት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ምርታማነትን በማሳደግና የገበያ እድሎችን በማስፋት ላይ ያተኮረ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት እንዲሁም በእሴት ሰንሰለቱ የሴቶችና ወጣቶችን አቅም በማጎልበት ምግብ ስርዓት ሽግግርን እውን ለማድረግ እየሰራች እንደሆነ አብራርተዋል።
በኃይለማርያም ተገኝ