በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት ጀመሩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
የክልሉየዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት ኃላፊ ዳኛ ፈዬራ ሀይሉ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ በክረምቱ በከፊል ዝግ የነበሩ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ውዝፍ መዝገቦችን በማጥራት እና የዜጎችን መብት ለማስከበር በተረኛ ችሎት አገልግሎት ሲሰጡ ነበር።
እነዚህ በክልሉ የሚገኙ 331 የወረዳ ፍርድ ቤቶች እና 25 ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በዛሬው ዕለት መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል።
ፍርድ ቤቶች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ለፍትህ ስርዓቱ ውጤታማነት ዳኞችና ደጋፊ ሰራተኞች የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገለጸዋል።
በክልሉ ቀደም ሲል አሮጌና ለዳኝነት አገልግሎት ምቹ ያልነበሩ የችሎት ማስቻያዎችን ምቹ በማድረግ የማስፋፊያና የማሻሻያ ስራዎች በተለያዩ ፍርድ ቤቶች እንዲሰራ ተደርጓል ነው ያሉት።
በታሪክ አዱኛ