Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በመድኃኒት ቁጥጥር የዓለም ጤና ድርጅትን 3ኛ ደረጃ የብቃት ማረጋገጫ ማግኘቷ…

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት 3ኛ ደረጃ የብቃት ማረጋገጫ (ማቹሪቲ ሌቭል ስሪ) ማሳካቷ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው።
የጤና ሚኒስቴር እና ኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ኢትዮጵያ በዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገራት የመድኃኒት ተቆጣጣሪ አካላት ምደባ ማቹሪቲ ሌቭል ስሪ ላይ መድረሷን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
“ማቹሪቲ ሌቭል ስሪ” የዓለም ጤና ድርጅት የሀገራትን የህክምና ምርቶች የመፍቀድ፣ የገበያ ክትትል እና የደህንነት ጉዳዮችን በብቃት የመቆጣጠር አቅማቸውን ገምግሞ የሚሰጠው የቁጥጥር ስርዓት የምደባ እውቅና ነው።
ኢትዮጵያ ያሳካችው ማቹሪቲ ሌቭል ስሪ በቀጣይ በመድኃኒት ቁጥጥር ዘርፍ ኢትዮጵያ ልትደርስበት ላቀደችው ስኬት ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ በመግለጫቸው ላይ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቀ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቷን ያረጋገጠ እና መንግሥትም የሕብረተሰብ ጤና ለመጠበቅ ያሳየውን ቁርጠኝነት የሚያጠናክር እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
እውቅናው ለዜጎች፣ ለጤና አገልግሎት አቅራቢዎች እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ኢትዮጵያ መድኃኒቶችን በብቃት የመቆጣጠር እና የማስተዳደር አቅም እንዳላት ያስመሰከረ እንደሆነም ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ እውቅናውን በማግኘት ከአፍሪካ ዘጠነኛ ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ደግሞ የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች ያሉት ሁለቱ ተቋማት÷ ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ማቹሪቲ ሌቭል ስሪ ማሳካቷ የተሻሻለ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ለማስፈን እንደሚረዳና ሌሎች ዓለም አቀፍ እውቅናዎችን ለማግኘት እንደሚያግዝ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ጥራት ያላቸው መድኃኒቶችን በተሻለ መንገድ ለማግኘት እንደሚያስችል፣ ጠንካራ የመድኃኒት ዘርፍ እንዲኖር እንደሚያደርግ፣ ለክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ትብብርና ድጋፍ በር እንደሚከፍት ጠቁመዋል።
ለሕዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ዝግጁነትን ያረጋግጣል፣ የአቅም ግንባታ እና ዘላቂነት ዕደገትን ያጎናፅፋል፣ ወደ ዓለም ጤና ድርጅት ማቹሪቲ ሌቭል 4 የሚወስድ መንገድ ለማምራት መደላድል ይፈጥራል እና በኢትዮጵያ የመድኃኒት ቁጥጥር ሥርዓት ላይ የሕዝብ አመኔታን ያጠናክራል የሚሉ ጠቀሜታዎችን አብራርተዋል።
ዓለም አቀፍ ትብብርን ያመቻቻል እና በሌሎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣናት መካከል እውቅና ያስገኛል፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ውጤታማ እና ጥራት ያላቸው መድኃኒቶችን በወቅቱ ማግኘትን ለማረጋገጥ የቁጥጥር ሂደቶችን ውጤታማነት ያሳድጋል ተብሏል።
ዕውቅናው ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በማሟላት እና ተወዳዳሪነትን በማሻሻል የሀገር ውስጥ ፋርማሲዩቲካል አምራቾችን እንደሚደግፍና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የህዝብ ጤና ላይ ያላትን ሚና የበለጠ ከፍ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.