Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማምጣት አብረን መስራት አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን ዓይናችንን ገልጠን በማየት በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማምጣት በጋራ አብረን መስራት አለብን አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል ለተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች መሰረተ ድንጋይ ባስቀመጡበት እንዲሁም ባስመረቁበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያን ለማስተዳደርና ለማልማት ያላትን ፍሬ እየበተንን ሳይሆን እየሰበሰብን መሆን አለበት ብለዋል።

በፈረንጆቹ በ1959 ዓ.ም ኢትዮጵያ አሰብ ወደብ አካባቢ 500 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማጥራት የሚችል የነዳጅ ማጣሪያ ገንብታ እንደነበር አስታውሰው÷ የነዳጅ ማጣሪያው ከ4 ዓመት በኋላ ወደ 800 ሺህ ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ማጥራት እንዲችል አድርጋ እንደነበር ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ማጣቷ ሀገር ለሚወድ ኢትዮጵያውያን የሚያንገበግብ ጉዳይ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

ከትላንት ጋር በጥቅሉ ሳንጣላ፤ ትላንትና ውስጥ መልካም ስራ ሲኖር ፈልቅቀን የምናሳድግ ስንክሳር ስህተት ሲኖር የምናርም ከሆነ አሰብ የተውነውን የነዳጅ ማጣሪያ ጥለን አንመጣም ነበር ብለዋል።

ቁጭታችንን በንዴት እና በለቅሶ ሳይሆን እንዲህ በተግባር በመስራት መወጣት አለብን ሲሉም አመላክተዋል።

ይህን አይነት ጥፋት ዳግም ላለመፈጸም ኢትዮጵያውያን ካለንበት መነታረክና መባላት ወጥተን እንደዚህ ባለው ታላላቅ ስራ የኢትዮጵያን ስም ማስጠራት እና ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር መስራት ይኖርብናል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ድፍን ዓለም ለኢንቨስትመንት የምትመች፣ ተስፋ ያላት ሀገር እያሉ በከፍተኛ ጉጉት ከእኛ ጋር ለመስራት በሚፈልጉበት እና በሚጠይቁበት በዚህ ጊዜ መላ ኢትዮጵያውያን ዓይናችንን ገልጠን በማየት በትብብር፣ በትግግዝ ሰላምን በማምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማምጣት በጋራ አብረን መስራት አለብንም ነው ያሉት።

የግመሉ ጉዞ በውሾች ጩኸት ስለማይደናቀፍ ጊዜያችሁንና ጉልበታችሁን ከምታባክኑ ከግመሉ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የብልጽግና ሩጫ እንድታፋጥኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እጠይቃለሁ ብለዋል።

ህልማችን ሩቅ ነው ተስፋችን የሚጨበጥ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ የምግብ ሉዓላዊነት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚረጋገጥ እና ለዚህ ደግሞ የአፈር ማዳበርያ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

የሶማሌ ክልልም ለዚህ አምቺ በመሆኑ የክልሉን እምቅ ሃብት በመጠቀም ክልሉን ለሶማሌ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካም የሚተርፍ ማድረግ እንችላለን ብለዋል።

በሶስና አለማየሁ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.