የሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ በድምቀት እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ከተማ ሀርሰዴ ሐይቅ በድምቀት መከበር ጀምሯል፡፡
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል “ኢሬቻ ለሀገር ማንሠራራት” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተከበረ የሚገኘው፡፡
በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ወጣቶች እና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡
የኢሬቻ ሀርሰዴ ‘የኢሬፈና’ (ምስጋና የማቅረብ) ሥነ ሥርዓት በአባገዳዎች ምርቃት በቢሾፍቱ ሀርሰዴ ሐይቅ ተከናውኗል፡፡
አባገዳዎችና ሃደሲንቄዎች በእጃቸው እርጥብ ሳር በመያዝ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን በማብሰር መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በሰላም በመጠናቀቁ ሁሉን ነገር ለፈጠረ አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበትና መጪው ዘመን መልካም እንዲሆን ፈጣሪን የሚለመንበት በዓል ነው፡፡