ባሕር ዳር በጠንካራ አመራርና ነዋሪዎች የጋራ ጥረት ውበቷ እየፈካ እና እየደመቀ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባሕር ዳር እንደ መስከረም ንጋት ውበት፣ ተስፋ እና ልማት ሆኖላት ተመልክተናል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ውሃ ከነውበት እና ስክነቱ፤ መልክዓ ምድር ከነ ለምነቱ፤ ልምላሜ ከነ ንጹህነቱ የታደለችው የውበት ምልክቷ ባህር ዳር በጠንካራ አመራርና ነዋሪዎች የጋራ ጥረት ውበቷ ይበልጥ እየፈካ እና እየደመቀች ነው ብለዋል።
በግዙፉ ዓባይ ላይ የተገነባው ባለግርማው ድልድይ ለባሕር ዳር ከድልድይም በላይ መለያ ቀለሟ፣ የቱሪዝም መዳረሻዋ መሆኑን ተመልክተናልም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት።
ባሕር ዳር ውበቷን እና ክብሯን የሚመጥኑ የመናፈሻ ስፍራዎች እየተገነቡ፤ የኮሪደር ልማቱም ከውበት የተሻገረ ልማት አሳላጭ ሆኖ በፍጥነት እና ፈጠራ እሴቶች እያማረች ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የብልጽግና ጉዟችን መዳረሻም እንደሀገር ወደሚመጥነን ከፍታ መሸጋገር ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።