ወጋገን ባንክ በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን 13 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ወጋገን ባንክ በ2017 በጀት ዓመት በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን 13 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ በማስመዝገብ የአንድ አክሲዮን ትርፍ ወደ 46 ነጥብ 1 በመቶ ማደጉን ይፋ አድርጓል፡፡
ወጋገን ባንክ አ.ማ. 32ኛ መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል፡፡
የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዲሹ ሁሴን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ባንኩ በ2017 በጀት አመት ያገኘው 13 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ በታሪኩ ከፍተኛ ሲሆን፥ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ38 በመቶ እድገት አለው፡፡
በተመሳሳይ ባንኩ ከታክስ በፊት በታሪኩ ከፍተኛ የሆነ የብር 3 ነጥብ 85 ቢሊየን ትርፍ ማግኘቱን ገልጸው፥ ካለፈው በጀት ዓመት የ73 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።
እስከ ሰኔ/2017 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ብዛት 14 ሺህ 871 መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፥ የባንኩ ጠቅላላ ካፒታል 12 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ደርሷል ነው ያሉት፡፡
የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 66 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መድረሱንና ጠቅላላ ሀብቱ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ወደ 84 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ማደጉንም ገልጸዋል፡፡