Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአፍሪካን ትርክት በመፍጠር ሂደት ጉልህ ሚና መጫወት ይጠበቅባታል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካን ትርክት በመፍጠር ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና መጫወት ኃላፊነቷ መሆኑ አይቀሬ ጉዳይ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የተሰኘውን የፓን አፍሪካ ሚዲያ በይፋ ስራ ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ሚዲያው በቀጣይ ዓመታት በአህጉሪቱ ከትልልቅ ሚዲያዎች አንዱ ይሆናል ብለዋል፡፡

የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ ስራ መጀመር ቀላል ጉዳይ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ቀደምትና ታዋቂ ከሆኑ ሚዲያዎች አንዱ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በቅርብ አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በብዙ ዘርፎች በአፍሪካ ግንባር ቀደም እንደምትሆን ጠቅሰው፥ በዚህም ምክንያት ትርክትን መገንባት የመሻት ጉዳይ ሳይሆን ኃላፊነት ይሆናል ነው ያሉት፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደጉ የመጡት መገናኛ ብዙሃን እድገታቸው ካቋቋሟቸው ሀገራት እድገት ጋር የሚገናኝ መሆኑን ጠቅሰው፥ ሀገራቱም በሚዲያዎቻቸው አማካኝነት ከራሳቸው አልፈው የዓለምን ትርክት ለመፍጠር እየሰሩ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ተነስታለች፣ እያንሰራራች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢኮኖሚያችን ይበልጥ እያደገ ሲሄድ የአፍሪካን ትርክት በመፍጠር ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና የመጫወት ኃላፊነት እንዳለባት ጠቁመዋል፡፡

በትርክት ሰው፣ ማህበረሰብ፣ ሀገር ብሎም አህጉር እንደሚሰራው ሁሉ በዚሁ ልክ በትርክት ግለሰብ፣ ማህበረሰብ እንዲሁም ሀገር ይፈርሳል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ብሎም አፍሪካ ከዚህ ቀደም በተገነባው ትርክት ምክንያት ትልቅ ሆነው ሳለ አንሰው እንዲታዩ በመደረጉ በአቅማቸው ልክ ሳይለሙ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

አፍሪካውያን ሰብሰብ ብለን እና ተደምረን የአፍሪካን ትልቅነትና የማድረግ አቅም በሚመጥን መልኩ ለውጥ ማምጣት እንደምንችል ይህ ሚዲያ ማሳያ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.