ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት የስትራቴጂያዊ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል የስትራቴጂያዊ አጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ በዲጂታላይዜሽን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በምግብ ሥርዓት፣ በጤና በመሰረተ ልማት እንዲሁም በሰላምና ጸጥታ ሁለቱ ወገኖች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡
ከስትራቴጂያዊ አጋርነት ስምምነቱ አስቀድሞ ፕሬዚዳንት ታዬ እና ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ በዚህ ወቅት ፥ የአውሮፓ ኅብረት “ግሎባል ጌትዌይ” መርሐ ግብር በኢትዮጵያ እና በኅብረቱ መካከል የጋራ ስትራቴጂያዊ ራዕይ ለመቅረፅና አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር በትክክለኛው ወቅት ይፋ መደረጉን አንስተዋል፡፡
ስምምነቱ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማሳደግ በፈረንጆቹ 2016 ለተፈረመው የስትራቴጂያዊ ትብብር ስምምነት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡