Fana: At a Speed of Life!

እስራኤል የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነትን አፀደቀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ የመጀመሪያውን ዙር የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነትን በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኒታንያሁ ጽ/ቤት እንዳስታወቀው÷ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ቀሪ የእስራኤል ታጋቾችን የሚያስለቅቅና ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡

በስምምነቱ መሰረት እስራኤል 53 በመቶ ከሚሆነው የጋዛ ክፍል ጦሯን የምታስወጣ ሲሆን፥ ሀማስ በበኩሉ 20 የእስራኤል ታጋቾችን በ72 ሰዓታት ውስጥ የሚለቅ ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ እስራኤል 250 እስረኞችንና በጋዛው ዘመቻ በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸውን ከ1 ሺህ 700 በላይ ሰዎች እንደምትለቅ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የሀማስ ከፍተኛ ባለስልጣን ኻሊል አል ሀያ በበኩላቸው÷ ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡት የተኩስ አቁም ስምምነት እቅድ ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ ነው ብለዋል፡፡

ታጣቂ ቡድኑ ለትራምፕ የተኩስ አቁም እቅድ ፈጣን አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱን ገልጸው፥ ስምምነቱ ያለምንም ችግር ተግባራዊ እንዲደረግ ከዋሽንግተን መተማመኛ አግኝተናል ነው ያሉት፡፡

ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ሀማስ በጋዛ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች ኃይሎች ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የእስራኤል እና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ምግብ፣መድሀኒት እና ነዳጅ ወደ ጋዛ ለማጓጓዝ ዝግጁ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.