ችሎትን የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሆኖ በመከታተል ፍትሕን ማግኘት ትልቅ ዕድል ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ችሎትን የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሆኖ በመከታተል ፍትሕን ማግኘት ትልቅ ዕድል ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያለማውን ስማርት የፍርድ ሥርዓት ተመልክተዋል።
ከምልከታቸው በኋላ በሰጡት ማብራሪያ፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራተጂ የተቀረጸው የፋይናንስ፣ የንግድ፣ የጸጥታ ተቋማትን ጨምሮ በርካታ ተቋማት የማሽን ግብዓት በመጠቀም አገልግሎትን እንዲያጠናክሩ መሰራቱን ገልጸዋል።
አገልግሎትን ለማሳለጥ በአስፈጻሚው በኩል እየተሰራ ያለው ስራ ከሌሎች የመንግሥት አካላት ጋር ካልተያያዙ አጠቃላይ የመንግሥት ቁመና እንደማያመጡ ጠቅሰዋል።
ፍትሕ በተለያየ መንገድ የሚገዛ በመሆኑ ፍትሕ እና ርትዕ አይረጋገጥም የሚል ስሞታ እንዳለ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ለመቀነስ አንዱ መፍትሄ ኦቶሜሽን ነው ብለዋል።
ችሎትን የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሆኖ በመከታተል ፍትሕን ማግኘት ትልቅ ዕድል እንደሆነ ገልጸው፤ ግለሰቦች ካሉበት ቦታ ሆነው ፍትሕን ማግኘታቸው ከጊዜና ከገንዘብ አንጻር የማይለካ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
ጠበቃው፣ ፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግ እና የዳኝነት ስርዓቱ ሲቀየር ሰዎች በቀላሉ ፍትሕ የሚያገኙበት ዕድል እየሰፋ ይሄዳል ነው ያሉት።
የዜጎች ትርፍ የሚለካው የተሳለጠ ፍትሕ በማግኘት እንደሆነ ጠቅሰው፤ የዘገየ ፍትሕ እንደ ፍትሕ የማይቆጠር በመሆኑ በፍጥነት በሕግ አግባብ የተገኘ መሆን አለበት ብለዋል።
ከዚህ አንጻር የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰራው ስራ አስደማሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአንድ ጊዜ በርካታ ችሎቶችን መቆጣጠር የሚያስችል ስራ መስራቱን ገልጸዋል።
ይህንን ልምምድ እና ስርዓት በቅርንጫፎች ማዳረስ ተችሏል፤ ከዚህም አልፎ ክልሎች ይህንን መንገድ እንዲከተሉ እያደረጉ ነው ብለዋል።
ብልጽግናን ማረጋገጥ ስናስብ ሁለንተናዊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብልጽግናው ፍትሕን እና የአኗኗር ዘይቤን ይመለከታል በማለት ተናግረዋል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረው ስራ ሁሉም ጋር ተዳርሶ ፍትህን ማጣጣም ያስፈልጋል ነው ያሉት።