ወንድማማቾቹ የመርከብ አዛዦች….
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በዛሬው ዕለት ካስመረቃቸው የመርከብ አዛዦች መካከል ሁለት ወንድማማቾች ይገኙበታል።
ወንድማማቾቹ የመርከብ አዛዦች ሚሊዮን ታሪኩ እና አቤል ታሪኩ ትውልድና ዕድገታቸው በአዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ነው።
ሚሊዮን እና አቤል ወደዚህ ዘርፍ የገቡት በተመሳሳይ የመርከብ አዛዥ የነበሩትን አባታቸውን ፈለግ ተከትለው ነው፡፡
አቤል ታሪኩ በልጅነቱ ወላጅ አባቱ አውሮፕላን አብራሪ እንዲሆን ቢፈልጉም እሱ ግን ምርጫው መርከበኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ለወላጅ አባቱ እያስረዳ እንዳደገ ተናግሯል።
ከልጅነቱ ጀምሮ መርከበኛ የመሆን ህልም የነበረው አቤል ይመኘው የነበረውን ነገር በማሳካት ህልሙን መኖር ከጀመረ እነሆ 14 ዓመታት ተቆጥረዋል።
የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ሚሊዮን በበኩሉ ወደዚህ ዘርፍ ከገባ 11 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፥ ስራውን እንደሚወድና ሀገሩን በዚህ ሙያ በስፋት ማገልገል እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡
ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት የሆነው ሚሊዮን የባህር ላይ ስራ ፈታኝ በመሆኑ ፅናትና ታታሪነትን ይጠይቃል ብሏል፡፡
መርከበኛ መሆን ለበርካታ ጊዜ ከቤተሰብ ጋር ተራርቆ መቆየትን እንደሚጠይቅ የሚገልጹት ወንድማማቾቹ የመርከብ አዛዦች፥ አባታቸው ለበርካታ ጊዜያት ከእነሱ ርቆ ባህር ላይ ይቆይ ስለነበር ከቤተሰብ ርቆ መቆየትን እንደለመዱት አስረድተዋል።
ሚሊዮን ለ18 ወራት እንዲሁም ወንድሙ አቤል ለ15 ወራት ያህል ባህር ላይ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በስራቸው ብዙ ማዕበልና ፈታኝ ጊዜያት እንደሚያሳልፉ የሚገልጹት ወንድማማቾቹ፥ የአባታቸው ድጋፍ ለዚህ ክብር እንዳበቃቸው ይናገራሉ።
የሀገራችን ወጣቶችም ወደዚህ ዘርፍ በመግባት ቤተሰባቸውን እንዲሁም ሀገራቸውን ከፍ ለማድረግ መስራት እንዳለባቸው ምክራቸውን ለግሰዋል።
በወንድማገኝ ፀጋዬ