ኢትዮጵያውያን አይቻልም የሚለውን እሳቤ መቀየር አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያውያን አይቻልም የሚለውን የተሰበረ አስተሳሰብ በመቀየር እንደምንችል ማሳየት አለብን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎችን በተመለከተ ከፌዴራልና ከክልል አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ በራስ አቅም አዲስ ነገር ከመፍጠር ይልቅ ከውጭ የማየት ልምምድና ባህል መኖሩን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የአይቻልም እሳቤ ብቻ ሳይሆን ተችሎ የተፈፀመውን ነገር የማመን ችግር መኖሩንም ነው የገለጹት፡፡
ለአብነትም በራስ አቅም የተሰሩ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም እንደተሰሩ ከማመን ይልቅ ከሌላ ሀገር ዲዛይንና የፋይናንስ ምንጭ ጋር የማያያዝ ሀሳቦች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ የእሳቤ ስብራት መንግስት በተግባር ቁም ነገር እንዳይሰራ የሚያደርግ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሌሎች ሀገራት ሳይመሰረቱ በፊት የበርካታ ስልጣኔዎች ባለቤት እንደነበረች አውስተው፥ ኢትዮጵያውያን የአይቻልም እሳቤን ሊቀይሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ