Fana: At a Speed of Life!

ጀግንነት ክላሽ ከማንገብ ይልቅ ሀገር በማልማት መገለጥ አለበት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጀግንነታችን መገለጥ ያለበት ክላሽ በማንገብ ሳይሆን ሀገር በማልማትና የህዝብን ኑሮ በማሻሻል ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፌዴራል እና ክልል አመራሮች ጋር በገጠር ኮሪደር ስራዎች ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ ጀግንነት የሚለው እሳቤ በተሳሳተ አውድ እየተተረጎመ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ጀግንነት ክላሽ አንግቦ መዞር ሳይሆን የደሀ እናትን ቤት በመስራት የሚገለጥ ነው ብለዋል፡፡

ጀግንነትን በተሳሳተ መንገድ ተገንዝበው ላልተገባ ዓላማ ጊዜ እና ጉልበታቸውን የሚያጠፉ ወንድሞቻችን የደሃ ወገኖቻችንን ህይወት ለመቀየር ሊሰሩ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጀግንነት ሀገርን በመለወጥና የህዝቡን ኑሮ በማሻሻል መገለጥ እንዳለበት ጠቅሰው፥ ይህን ማድረግ ከቻልን ከልመና መውጣት እንችላለን ነው ያሉት፡፡

በቅርቡ ከልመና ነጻ ለመውጣት ህዝብ በማወያየት ስራ ጀምረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አብዛኞቹ ክልሎች እነዚህን ስራዎች በይፋ ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአንዳንድ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖሪያቸው በመመለስ ሰርተን ህይወታቸውን በመለወጥ ኢትዮጵያን ባጠረ ጊዜ ከልመና ማውጣት እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡

ሰዎችን አፈናቅሎ ማፈን እንደ ፖለቲካ እየታየ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከዚህ አስተሳሰብ ወጥተን በሀገር ደረጃ የሚጨበጥ ለውጥ በማምጣት ልጆቻችን ከችግርና ጦርነት ተላቀው በሰላም እንዲኖሩ ማድረግ እንችላለን ነው ያሉት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.