የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከኩዌት ፈንድ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) አመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን ከኩዌት ፈንድ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ዋሊድ አል ባሃር ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና ኩዌት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ስለማጠናከር እንዲሁም ኢትዮጵያ እየተገበረችው የሚገኘውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተመለከተ መክረዋል፡፡
በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የልማት ዘርፎችና በኩዌት ፈንድ ድጋፍ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት የእዳ ቅነሳ ሂደትን ጨምሮ መንግስት ያከናወናቸውን የሪፎረም ስራዎች እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቁልፍ የልማት ስራዎችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ አዲስ ለምትገነባው ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተወያዩ ሲሆን፥ በመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ላይ የኩዌት ፈንድ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
የኩዌት ፈንድ ዳይሬክተር አል ባሃር በበኩላቸው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ራዕይ አድንቀው፥ በኢኮኖሚ ማሻሻያው እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል፡፡
ተቋማቸው ግዙፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ላሉ የልማት ስራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች ትብብራቸውን ለማጠናከርና ተቋሙ በኢትዮጵያ ከፍተኛ አበርክቶ ላላቸው የልማት ስራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥል ተስማምተዋል፡፡