Fana: At a Speed of Life!

እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ትውልድን ያስተሳሰረ የወል አጀንዳ – የባህር በር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህር በር ጉዳይ ልክ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትውልድን ያስተሳሰረ የወል አጀንዳ መሆን ችሏል፡፡
ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ የነበራት ድርሻ የጎላ ነበር።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አባል ፔቲ ኦፊሰር ታየ ሐረሩ እንደሚሉት፥ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ከ36 አመታት በኋላ ትኩረት ማግኘቱ ተገቢነት ያለው ጉዳይ ነው፡፡
ፔቲ ኦፊሰር ታየ ለ12 ዓመታት በባህር ኃይል መርከበኛ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፥ ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ አንዱ የመተንፈሻ አካሏ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት የባህር በር አልባ ሆና መቆየቷ የሚይስቆጭ መሆኑን ገልጸው፥ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ ማሪታይም ማሰልጠኛ ተቋም ስር ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በኮሎምቢያ ሺፕ ማኔጅመንት ያገለገለው ኦፊሰር ቃልኪዳን አሰፋ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ያለ ባህር በር መቆየቷ ፍትሐዊ አለመሆኑን ገልጿል፡፡
15 በመቶ የዓለም የንግድ መርከብ ፍሰት በቀይ ባህር ላይ እንደሚካሄድ ጠቅሶ፥ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በቅርብ ርቀት ላይ ሆና እስካሁን የበይ ተመልካች መሆኗ ተገቢ አይደለም ብሏል፡፡
በቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት ማሳካት ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ መሆኑን የሚገልጹት መርከበኞቹ፥ ለንግድ፣ ለሰላምና ደህንነት እንዲሁም በቀጣናው ያላትን ተጽዕኖ ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ህጋዊና ተፈጥሮዊ መብት መሆኑን ጠቅሰው፥ በሙያቸው ሀገራቸውን ለማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የባህር በር ጉዳይ ልክ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትውልድን ያስተሳሰረ የወል አጀንዳ መሆኑን አንስተዋል።
በወርቅአፈራው ያለው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.