Fana: At a Speed of Life!

የድሮን ቴክኖሎጂ ማምረቱን አጠናክሮ የቀጠለው ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የድሮን ቴክኖሎጂዎችን ማምረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል አሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ሲሳይ ቶላ፡፡
ኢንዱስትሪው ማምረት የጀመራቸውን ድሮኖች ምርት በማስፋት የድሮን ቴክኖሎጂን በምርምርና ሥርጸት ለማሳደግና ተግባራዊ ተሞክሮን ለማዳበር ከተለያዩ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የተፈራረመው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኢፌዴሪ አየር ኃይል፣ ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ምክትል ዳይሬክተር ጄነራሉ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ብሔራዊ ጥቅምን ከማስከበር እንዲሁም ካለው የላቀ ኢኮኖሚያዊና ስትራቴጂያዊ ፋይዳ አንጻር የድሮን ቴክኖሎጂን በራስ አቅም ማልማት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡
ይህን ከግምት በማስገባት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ የጀመረው ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንደስትሪ ለደኅንነት፣ ለመረጃ ስምሪት፣ ለሲቪልና ለወታደራዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ድሮኖች ምርትን አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ በሚያደርጋቸው ምርምር እና ልማት እንዲሁም የሰው ኃይልን በማሰልጠን ከስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንደስትሪ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንደስትሪ የሚመረቱ ድሮኖችን መጠቀም የሚችልበት ዕድሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዘርፉን በራስ አቅም በተገቢው መንገድ ለመጠቀም በትብብር ለመስራት አጋጣሚው ተፈጥሯል ያሉት ደግሞ የመከላከያ ኢንጂነሪግ ኢንደስትሪ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታቸው ሃይለማርያም ናቸው፡፡
የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ የጀመረው ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንደስትሪ ለደኅንነት፣ ለመረጃ ስምሪት፣ ለሲቪልና ለወታደራዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ድሮኖች ምርት ማምረቱን አጠናክሮ መቀጠሉ ነው የተገለጸው፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.