Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለኢትዮጵያ የ110 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገባ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ ለገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮግራም የሚውል የ110 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል፡፡

ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የዓለም አቀፍ አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄነራል ማሪያታ ጃገር እና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የዓለም አቀፍ አጋርነት ዳይሬክተር ቱራያ ትሪኪን ጋር በተደረገው ውይይት ትብብን ለማጠናከር መክረዋል።

ውይይቱ በዋናነት ቀጣናዊ የመሰረት ልማት ትብብን ለማጠናከር እንዲሁም በተለያዩ ማሻሻያዎች ላይ የሚደረገውን የፋይናንስ ድጋፍ ለማጠናከር ያለመ ነው።

በውይይቱ አቶ አህመድ ሺዴ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እና በሴቶች የስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡

በቀጣይም ባንኩ በገጠር አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት (RISED) ኢኒሼቲቮች እንዲሁን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ቱራያ ትሪኪን በበኩላቸው÷ ተቋማቸው ለገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮግራም (RUFIP III) ሶስተኛ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ የሚውል የ110 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደረግ ገልፀዋል፡፡

ውይይቱ የኢትዮጵያ መንግስት እና የአውሮፓ ህብረት ተቋማት በዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ልማት ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ተብሏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.