Fana: At a Speed of Life!

የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን ከራስ ታሪክ ጋር የመታረቅ ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን ከራስ ታሪክ ጋር የመታረቅ ጉዳይ ነው አለ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፡፡
የዓባይና ቀይ ባሕር ትስስር እና የአፋር ክልል ሚና በሚል መሪ ሃሳብ በሰመራ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በታሪክ አጋጣሚ ያጣነውን የባሕር በር አሁን ላይ አጥብቀን መሻታችን ራስን የመሆንና የመፈለግ፤ ከራስ ታሪክና ማንነት ጋር እርቅ የመፈጸም ጉዳይ ነው፡፡
የባሕር በር ጉዳይ ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በሕግ፣ በተፈጥሮና ጂኦፖለቲካዊ እውነታዎች የሚገባትን ቦታ የማግኘት እንዲሁም የሚጠበቅባትን ጂኦፖለቲካዊ ሚና የመወጣት ጉዳይ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ‎መሃመድ ኡስማን በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያ ሕልውና በዓባይ እና በቀይ ባሕር ላይ የተመሰረተ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው መጠነ ሰፊ ጥረት ጠቀሜታው ለቀጣናው ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ የሆነችው ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘቷ ጉዳይ ለነገ የሚባል እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ የተደረገው የዲፕሎማሲ ተጋድሎ በቀይ ባሕር ላይ ሊደገም እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
በቀይ ባሕር ጉዳይ ካሁን ቀደም በርካታ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የሕይወት ዋጋ ከፍለዋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ም/አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ኮሞዶር ተገኝ ለታ ናቸው፡፡
የአሁኑ ትውልድም የባሕር በር ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የራሱን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በአመለወርቅ መኳንንት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.