ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክር ሒደቱ ያላቸው ቁልፍ ሚና…
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክር ሒደቱ ቀልፍ ሚና አላቸው አለ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፡፡
ኮሚሽኑ በወላይታ ሶዶና ቦንጋ ከተሞች ከሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኛ የማሕበረሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
በቦንጋው መድረክ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች በምክክር ሒደቱ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው አውስተው÷ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ በትኩረት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
መርሐ ግብሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ስለ ሀገራዊ ምክክር ሒደትና ሁኔታ ግንዛቤ አግኝተው ለቀጣይ የኮሚሽኑ ሥራ ግብዓት እንዲሰጡ ለማስቻል ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ በሕብረተሰቡ ዘንድ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግና ያለመውን ግብ ለማሳካት ሴቶች ፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በወላይታ ሶዶው የውይይት መድረክ የተገኙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን በበኩላቸው÷ ሀገራዊ ምክክሩ አካታች በሆነ መንገድ ብዙ ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉበት አስረድተዋል፡፡
ምክክሩ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ መስማማት ላይ ብቻ የሚያተኩር ሳይሆን ተጨባጭ ለሆኑ እና መተማመንን ለሚፈጥሩ መግባባቶች መደላደል የሚፈጥር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አለመግባባትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለሚደረገው ጉዞ የውይይት መድረኩ ወሳኝ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በጌትነት ጃርሳ