Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያን የለውጥ አጀንዳ ይደግፋል – ሲዲ ታህ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ሲዲ ኦልድ ታህ (ዶ/ር) ተቋማችን የኢትዮጵያን የለውጥ አጀንዳ ይደግፋል አሉ።

ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከባንኩ ፕሬዚዳንት ሲዲ ኦልድ ታህ(ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም አቶ አህመድ ሺዴ በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት ከባቢን ምቹ የማድረግ፣ ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ምርታማነትን የማሳደግ እና የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ አቅምን ለማጠናከር ያለሙ የሪፎርም ስራዎችን አስመልክተው ገለፃ አድርገዋል።

በአዲሱ ግዙፍ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ አዳዲስ መረጃዎችን ያካተተ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን የአፍሪካ ልማት ባንክ ፋይናንስ በመስጠት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።

ሲዲ ታህ (ዶ/ር) የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ ያለዎት ያሉ ሲሆን በአመራር ሰጭነታቸው ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልፀው፤ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።

ፕሬዚዳንት ሲዲ ኦልድ ታህ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ እና የሪፎርም አጀንዳዎች አፈፃፀም አድንቀዋል።

ባንኩ የሀገሪቱን ትልቅ የለውጥ አጀንዳ በበጀት ድጋፍ፣ በግብርና እና በመሰረተ ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ በተለይም የአየር ትራንስፖርት ትስስርን በማጠናከር የቀጣናዊ ትስስርና ውህደት እንቅስቃሴዎች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.