የጋራ ሥራችን ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች በመግለጥ ለቀጣዩ ትውልድ መሠረት መጣል ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋራ ሥራችን ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች መግለጥ፣ ማሳደግና በሀብቶቹ ላይ በመጨመር ቀጣዩ ትውልድ ችቦውን ተረክቦ እንዲቀጥል መሠረት መጣል ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ አመራሮች ጋር በመሆን በባሌ ዞን እያደረጉት በሚገኘው ጉብኝት የመጨረሻ መዳረሻቸው የሆነውን አስደማሚው የፊንጫ ሀበራ ፏፏቴ ተመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንዳሉት፥ ባለፉት ሶስት ቀናት በጉብኝቱ የተሳተፉ የቀድሞና በሥራ ላይ ያሉ ኃላፊዎች የተመለከቱት የተፈጥሮ፣ የባሕልና የሰው ኃብት ከፍ ያለ መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል።
ኢትዮጵያ ለሁሉም የሚበቃ ሀብት እንዳላት እናውቃለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የጋራ ሥራችን እኚህን ሀብቶች መግለጥ፣ ማሳደግ፣ በሀብቶቹ ላይ በመጨመር ቀጣዩ ትውልድ ችቦውን ተረክቦ እንዲቀጥል መሠረት መጣል ነው ብለዋል።
በግርማ የሚወርደው ፏፏቴ ወደ ሶፍኡመር የዋሻ ሥርዓት የሚደመረውን የወይብ ወንዝ የሚቀላቀል መሆኑን ጠቅሰው፥ አካባቢው የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ እና ድንቅ የአዕዋፍ መገኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በቅርቡ የዋሻ መስህብ የተገኘበት እንዲሁም የራፉ ውብ የዐለት ደን አቅራቢያ የሚገኝ መሆኑን ገልጸው፥ በቅርቡ በአካባቢው የሚገነባው ማረፊያ ሲጠናቀቅ ለጎብኝዎች የበለጠ ሳቢና ምቹ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በርግጥም የተትረፈረፈ ሀብት ምድር መሆኗን በማውሳት እንሰባሰብ፣ ለማለም እንድፈር፣ የጋራ ነጋችንን በጋራ እንገንባ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡