Fana: At a Speed of Life!

ከ107 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት 107 ሺህ 191 አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት።

የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ አፈጻጸሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ18 ነጥብ 3 ከመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡

የአግልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት አዳዲስ ደንበኞች መካከል 95 ነጥብ 5 በመቶ የድህረ ክፍያ ሲሆኑ÷ 4 ነጥብ 5 በመቶ ደግሞ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ደንበኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አኳያ 14 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡

ከእዚህም መካከል 13ቱ ከዋናው ግሪድ እንዲሁም አንድ መንደር በኦፍግሪድ (በፀሐይ ኃይል አማራጭ) ተጠቃሚ እንደሆኑ አመልክተዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝነትና ጥራትን ለማሻሻል 957 ኪ.ሜ የዲስትሪቡዩሽን መስመሮች የመልሶ ግንባታ ስራ፣ 2 ሺህ 151 ኪ.ሜ የማስፋፊያ ስራ፣ የ493 ነባር ትራንስፎርመሮች ማሻሻያና 850 አዲስ ትራንስፎርመሮች ተከላ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

ሥነምግባርና ብልሹ አሰራርን ከመከላከል አንፃር በ20 ሰራተኞች ላይ ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ እና የዲሲፕሊን እርምጃዎች ተወስዷል ነው ያሉት፡፡

የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ለማጠናከር እየተደረገ ባለው ጥረት በኢ-ፔይምነት ክፍያ የፈፀሙት ደንበኞች ቁጥር 94 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.