ዳያስፖራዎች በንቃት የተሳተፉበት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት…
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያዩ ሀገራት ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ጋር የተደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ስኬታማ ነበር አለ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፡፡
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ የሀገራዊ ምክክር ሒደቱን ይበልጥ አካታች እና አሳታፊ ለማድረግ የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በዚህ መሰረትም ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ ሀገራት ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ጋር በአካል የተደረገው አጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሒደት በስኬት መጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡
የውይይት መድረኮቹ በሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ ስዊዲን፣ እንግሊዝ እና በደቡብ አፍሪካ ነው የተካሄዱት፡፡
በምክክሩ ዳያስፖራዎች ለሀገራዊ መግባባት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት በቀናነትና በንቃት መሳተፋቸውን ነው ያስረዱት፡፡
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ያለመግባባትና የሀሳብ ልዩነነት ምንጭ ናቸው ያሏቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በተለያዩ ሀገራት በተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደትም ለምክክሩ ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎችን ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በተካሄዱ መድረኮች ዳያስፖራዎች በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን መምረጣቸውን አንስተዋል፡፡
ዳያስፖራዎች ልዩነትን ከሃይል አማራጭ ይልቅ በመወያየት መፍታት ይሻላል በሚል ላደረጉት ንቁ ተሳትፎም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ከአጀንዳ ማሰባሰቡ ጎን ለጎን የኮሚሽኑ አመራሮች ከተለያዩ ሀገራት የዘርፉ ተቋማት አመራሮች ጋር በመወያየት በሀገራዊ ምክክር ሒደት ላይ ተሞክሮ መጋራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሀገራዊ ምክክር ሒደቱ እስካሁን በ11 ክልሎች፣ በሁለት ከተማ አስተዳድሮች፣ በፌዴራል ተቋማትና ከዳያስፖራው ጋር ውይይት በማካሄድ አጀንዳ የመሰብሰብ ሒደት መከናወኑ ተመልክቷል፡፡
በመላኩ ገድፍ