የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳ ለማሳደግ የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ ነው – አቶ አህመድ ሺዴ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳ ለማሳደግ ከፍተኛ የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ገለጹ፡፡
በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ባለው የአለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ግሩፕ አመታዊ ስበሰባ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ጉዳዮች ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ብጄርዴ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በቅድመ-ልማት ፕሮጀክቶች፣ በመካሄድ ላይ ባሉ የሪፎርም ስራዎች እና አዳዲስ የፋይናንሲንግ ዘዴዎች ላይ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ውይይት አደርገዋል።
አቶ አህመድ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ታላቅ የልማት አጀንዳ ለማሳደግ ያለውን ከፍተኛ ሚና እውቅና በመስጠት እየተደረገ ለሚገኘው ከፍተኛ የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ባንኩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማዘመን፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ አዳዲስ የእድገት መንገዶችን በመፍጠር እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን በማጎልበት የስራ እድል ለመፍጠር እና በመላ ሀገሪቱ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል ያለውን አስተዋፅዖ አመላክተዋል።
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ አጋርነት እና ከፍተኛ ድጋፍ እየተካሄዱ በሚገኙ ዋና ዋና ዘርፎች ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ድጋፍን በማረጋገጥ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የስራ እድል ፈጠራን፣ ዘላቂ መሠረተ ልማቶችን እና የሰው ሃይል ካፒታል ልማትን ለማስቀጠል የባንኩ ቀጣይ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
አና ብጄርዴ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባካሄደው የሪፎርም አጀንዳ ጉልህ እድገት መገኘቱን አንስተዋል፡፡
የዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን በማብራራት ከፍተኛ የወጪ ንግድ መጨመሩን ተረድተናል ብለዋል፡፡
በተለይም በወርቅ፣ የተሻሻለ የሀገር ውስጥ ገቢ ማሰባሰብ፣ የፊስካል ማገገምን የሚያጠናክር እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ ምቹ የንግድ ሁኔታን እየተፈጠረ መሆኑን በመግለፅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዋና ዋና የየሪፎርም ርምጃዎችን በመተግበር ረገድም መንግስት የተጀመረውን ጠንካራ እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያበረታቱም ጠቁመዋል።