በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 401 ሺህ ኩንታል የበርበሬ ምርት ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የበርበሬ ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወነው ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ ፡፡
በቢሮው የቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ቶፊቅ ጁሃር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በክልሉ ለቡናና ቅመማ ቅመም ያለውን ምቹ ሁኔታ ይበልጥ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው፡፡
በርበሬ፣ ዝንጅብል፣ ሮዝመሪ፣ ሚጥሚጣ፣ ኮሰረት እና እርድ በክልሉ በብዛት የሚመረቱ ቅመማ ቅመሞች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በ2017/18 ምርት ዘመን በመኸር እርሻ በተለይም የበርበሬ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት መሰራቱን ነው የገለጹት፡፡
በዚህ መሰረትም የክልሉ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የበርበሬ ሰብልን በስፋት መልማታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽና የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማሰራጨት የክልሉ አርሶ አደሮች በርበሬ እንዲያለሙ መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ ከ30 ሺህ 100 ሄክታር በላይ መሬት በበርበሬ ምርት መሸፈኑን ጠቁመው ÷ ከዚህም ከ401 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
የምርት አሰባሰብ ሒደቱ በቅርቡ በስፋት እንደሚጀመር የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ÷ የምርት ብክነት እንዳይከሰት አርሶ አደሩ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ