የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት የሆነው ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ጉዳይ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ሀገራዊ አንድነትና ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል አሉ ምሁራን።
ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር እንዲሁም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተማራማሪ ጥላሁን ሊበን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት በበርካታ የመንግሥት ስርዓቶች ብሔራዊ ጥቅሟ ተፅዕኖ ውስጥ ገብቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
ብሔራዊ ጥቅም የመንግሥት ወይም የፓርቲ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች ልዩነቶች ቢኖሩም የውስጥ አንድነትን በማረጋገጥና በመከባበር ሁሉም ዜጋ ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ተመራማሪ አዲስ አለማሁ በበኩላቸው÷ ከለውጡ መንግሥት በኋላ እንደ ባሕር በር፣ አካታች ዴሞክራሲ እና ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የመሳሰሉ ወሳኝ የብሔራዊ ጥቅም እሳቤዎች ወደ ፊት መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ነጠላ ትርክት የወለዳቸው ችግሮች ለሀገራዊ ጥቅም መረጋገጥ ፈተና እየሆኑ መምጣታቸውን አመላክተዋል።
በተለይም የማህበራዊ ሚዲያው ከወል ትርክቶች ይልቅ ነጠላ ትርክቶችን በማጉላት ከብሔራዊ አንድነት ይልቅ ልዩነቶች እንዲሰፉ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ስታድግ ሁሉም ዜጋ አብሮ እንደሚያድግ በመግለጽ ዜጎች የሀገራቸው አምባሳደር ሊሆኑ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ