የባህር በርን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ስብራቶችን ለመጠገን ከባለድርሻዎች ጋር በትጋት ይሰራል – ብልፅግና ፓርቲ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የባህር በርን ጨምሮ ቀሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ስብራቶችን ለመጠገን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትጋት ይሰራል አለ።
የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት፤ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮችና የፓርቲ አጀንዳዎች ላይ መክሮ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና የማረጋገጥ ራዕይን ሰንቆ ወደ ተግባር የገባው ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ለህዝብ ቃል የገባውን በውጤታማነት እየፈጸመ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ቀሪ ስብራቶች ለመጠገን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትጋት እንደሚሰራ ተናግረው፤ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረጉ የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ገልፀዋል።
ባለፉት ዓመታት በተሠሩ የልማት ስራዎች ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ውጤት መምጣቱን ገልጸው፤ ለአብነትም ባለፈው ዓመት የ9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እየተረጋገጠ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው መገምገሙን ጠቅሰው፤ በዚህም ኢኮኖሚው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪና ዘመናዊ አገልግሎት እየተሸጋገረ ይገኛል ብለዋል።
በገቢ ማሰባሰብ፣ በወጪ ንግድ እና በተኪ ምርት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን በማንሳት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ፈጣን ብቻ ሳይሆን አካታች፣ ጥራት ያለውና የህዝቡን ኑሮ በተጨባጭ እያሻሻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በተጀመሩ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸው፤ በሰው ተኮር ስራዎችም በርካታ አቅመ ደካማ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም ተረጂነትን የማስወገድ፣ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት በቂ ፈንድ የመያዝ እንዲሁም ብሔራዊ የመጠባበቂያ ክምችትን በራስ አቅም የማምረት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሰላም እና የፖለቲካ ጉዳዮችን መገምገሙን በማንሳት ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የበኩሉን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑን ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።
መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተአማኒ፣ ግልጽና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ፓርቲው የድርሻውን እንደሚወጣም ገልጸዋል።
ውስን የሰላምና ፀጥታ ችግር የነበረባቸውን አካባቢዎችን ለማረጋጋት መንግስትና ህዝብ በጋራ በሰሩት ስራ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
የፖለቲካ ጥያቄ ያለው ማንኛውም አካል ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ምህዳር መፈጠሩን ገልጸው፤ ፓርቲውና የሚመራው መንግስት ሁልጊዜም በራቸው ለሰላም ክፍት ነው ብለዋል።
በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ለማድረግ የተቀመጠው አቅጣጫ ወደ ተጨባጭ ተግባር መግባቱን ተገምግሟል ነው ያሉት።
በዚህም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የማስፋትና የዲጂታላይዜሽን ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን አመልክተው፤ እስካሁንም 16 ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሠጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሶብ ማዕከላት የህዝቡ እርካታ ወደ 95 መቶ መድረሱን ገልጸው፤ ማዕከላቱን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ 100 ለማድረስ እንዲሰራ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ጠንካራ መንግስትና ሀገር ለመገንባት የያዘውን ግብ ለማሳካት የአመራርና አባላቱን አቅም የሚያጎለብቱ የተለያዩ ተግባራትን እንዳከናወነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አመራርና አባላቱ በተሠጣቸው ተልዕኮ ልክ በየደረጃው የመገምገም ስራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፤ በምዘናው መሠረት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡት እውቅና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የተሰጣቸውን ሀገራዊና የፓርቲ ተልዕኮ በአግባቡ ባልተወጡ አመራሮች ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን መወሰዱን ተናግረው፤ ፓርቲው ህዝብና ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመራችውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።