Fana: At a Speed of Life!

ካምፕ እንጂ ፕሮጀክት ያልነበረው የኮይሻ ግድብ አሁን በ128 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ካምፕ እንጂ ፕሮጀክት ያልነበረው የኮይሻ ግድብ አሁን በ128 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምልከታ በኮይሻ’ በሚል ርዕስ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ውይይት በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ገለጻ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮይሻ ግድብ መኖሩን የሰማሁት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 1 ቢሊየን ዩሮ ሳሊኒ በሦስተኛ ወገን አስወስኗል ተብሎ ከእሱ ጋር ድርድር ሳደርግ ነው ብለዋል።

ከዚያም ሳሊኒንን ጨምሮ ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ወደ ኮይሻ ሲያቀኑ ካምፕ እንጂ ፕሮጀክት እንዳልነበር መመልከታቸውን አስታውሰው፤ አንዲት ኪሎ ሲሚንቶ ፕሮጀክቱ ላይ እንዳልተጨመረ ተናግረዋል።

በአንጻሩ ለግድብ ሥራ የሚያግዙ ልል አፈሮች ለማውጣት መጠነኛ ቁፋሮ የተጀመረ ቢሆንም እሱም በገንዘብ እጥረት ተቋርጦ እንደነበር አንስተዋል።

በወቅቱ የፕሮጀክቱን ጠቃሚነት ተረድተው ወደ ጊቤ 3 በመሄድ ትስስሩን እና አስፈላጊነቱን መመልከታቸውን ጠቅሰው፤ ይህንን ጉዳይ እንዴት አድርገን ልናስጀምርና ልናሳካ እንደምንችል ተመካከርን ብለዋል።

የኤሌክትሪክ ፍላጎትና አቅርቦትን ለማመጣጠን ከፍተኛ ሚና እንዳለው በማመን ፕሮጀክቱ እንዲጀመር ውሳኔ ማሳለፋቸውን አውስተዋል።

ለግድቡ፣ ለስፒል ወይ እና ለፓወር ሀውስ ሥራ የሚውል 15 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ ልል አፈር ተዝቆ መውጣቱንም ገልጸዋል።

ይህ ከሆነ በኋላ 5 ነጥብ 4 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር ኮንክሪት ተሠርቷል፤ ይህ የሆነው ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታ አብዛኛው ግብዓት ተጓጉዞ መድረሱን ተናግረዋል።

አሁን የኮይሻ ግድብ ከሕዳሴ ግድብ በ17 ሜትር ዝቅ ብሎ በ128 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

ከኢትዮጵያውያን የተደመረ ጥረት ውጭ ስለወሰንን እና ገንዘብ ስለመደብን ብቻ ፕሮጀክት ማሳካት አይቻልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፕሮጀክት ቁርጠኛ ሙያተኞችና የሚጠብቀው ሰላም ወዳድ ማኅበረሰብ እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

በኮይሻ የተሳተፉ ባለሙያዎች፣ ሠራተኞች ፕሮጀክቱ የሚገኝበት አካባቢ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የኮይሻ ፕሮጀክት ለቀጣይ ሥራዎች ዐቅም በሚሆን መልኩ በዕውቀት ሽግግር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው፤ ይህም አኩሪ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.