Fana: At a Speed of Life!

የኮይሻ ፕሮጀክቶች መንግስት ለሀገራዊ ፀጋዎች የሰጠውን ትኩረት ያሳያሉ – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮይሻ ፕሮጀክቶች የለውጡ መንግስት ሀገራዊ ፀጋዎችን ለማልማት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያሉ አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‘የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምልከታ በኮይሻ’ በሚል ርዕስ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ውይይት በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ÷ የኮይሻ ፕሮጀክት በጥቂት ጊዜያት የግንባታ ሂደቱ በሚያምር መልኩ መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም ኮይሻ ግድብ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን አስገራሚ የቱሪዝም መስህቦችን የያዘ አካባቢ ነው በማለት ገልጸዋል።

አካባቢው የኦሞ ወንዝ፣ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን እንዲሁም የተለያዩ ተራራዎችን እና ወንዞችን የያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአካባቢው ሎጆች እና መዝናኛ ስፍራዎች ሊገነቡ ይችላል ብለዋል።

በመሆኑም ኮይሻን፣ ሀላላ ኬላን እና ጨበራ ጩርጩራን በማስተሳሰር የአካባቢውን የቱሪዝም ፀጋ በአግባቡ መጠቀም እንደሚስፈልግ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ኮይሻ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ በስኬት የተጠናቀቀ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተው፤ ፕሮጀክቱ መንግስት ሀገራዊ ፀጋዎችን ለማልማት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ለተሳተፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሰጡት አመራር ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.