Fana: At a Speed of Life!

በሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን ማስቀጠል ችለናል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ችግሮች በሚታዩበት ዐውድ በሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን ማስቀጠል ችለናል አሉ በምክልት ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ።

‘የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምልከታ በኮይሻ’ በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ውይይት በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር አድርገዋል።

አቶ አደም ፋራህ በወቅቱ እንዳሉት፤ በጂኦፖለቲካ ውጥረት፣ ኢተገማች በሆነው የታሪፍ ዲፕሎማሲ እና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ችግሮች በሚታዩበት ዐውድ ሁኔታ በኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን ማስቀጠል ተችሏል።

ይህም የሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ድምር ውጤት መሆኑን ገልጸው፤ የመጀመሪያው ከለውጡ ወዲህ የተፈጠረው የዕይታ ለውጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በመደመር እሳቤ ሁሉንም አቅሞች ደምረን በእያንዳንዱ ዘርፍ ለሀገር እድገት እና ብልጽግና እንዲያበረክት ለማድረግ ሰርተናል ብለዋል።

በዚህም ለኢትዮጵያ የሚመጥኑ ዕቅዶችን በመያዝ፣ በመፍጠን እና መፍጠር መርህ በመስራት ብሎም ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የታቀዱትን በስኬት ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስ የሚል እሳቤ ተይዞ በመሰራቱ የመጣ ውጤት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአመራር የማስፈጸም አቅም ትጋት እና ቁርጠኝነት ሁለተኛው ጉዳይ እንደሆነ አንስተው፤ ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራሩ በየአካባቢው ያለውን ጸጋ እና የመልማት ዕድል በማየት እንዲያለማ አረዓያ ሆነዋል ብለዋል።

መሰራት የሚገባው ስራ በተሻለ መንገድ መታቀድ በመጀመሩ እና አመራሩ ፕሮጀክቶችን መከታተል መጀመሩ ለዚህ ውጤት አብቅቶናል ነው ያሉት።

በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የህዝቡ፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማሕበረሰቡ ተሳትፎ እና ትብብር ማደግ አስተዋጽዖ ማድረጉን ገልጸው፤ ለዕድገት እና ብልጽግና ያላቸውን ሚና ከመጫወት አኳያ ትልቅ ለውጥ መምጣቱን አስረድተዋል።

ከህዝብ ጋር በመወያየት የሚቀርቡ ጥያቄዎችን እንደ ግብዓት ወስዶ በመስራት ከማህበረሰቡ ጋር ተግባብቶ የመስራት ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ሕዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩትን የኑሮ ውድነትን ማቃለል፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ማድረግ፣ ከሰላም እና ጸጥታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መንግስት በአግባቡ ከሕዝብ ጋር በመሆን ችግሮቹ እንዲቃለሉ ርብርብ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.