የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለእንቅስቃሴ ምቹ የከተማ ሥፍራዎች እየፈጠሩ ይገኛሉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለእንቅስቃሴ ምቹ የከተማ ሥፍራዎች እየፈጠሩ ይገኛሉ አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የተጠናቀቀውን የሳር ቤት-ጀርመን አደባባይ-ጋርመንት እና ፉሪ አካባቢ የኮሪደር ልማት ሥራ ጎብኝተናል ብለዋል።
ከ589 ሄክታር በላይ የሚሸፍነው ከባቢ ከካዛንቺስ ቀጥሎ ሰፊው የልማት ስፍራ ሆኗል በማለት ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ 16 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ የ3 ኪሎ ሜትር ተጨማሪ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ብሎም 33 ኪሎ ሜትር የተዘረጋ የእግረኛ መንገድ አካትቷል ነው ያሉት።
የፕላዛዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎች እና 5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራ መከናወኑንም አንስተዋል።
የመኪና ማቆሚያዎች፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ስፍራዎች፣ በግል እና የመንግሥት ተቋማት የተገነቡ 1 ሺህ 107 ሱቆች በልማት ሥራው ተሰርተዋል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ 50 ነጥብ 5 ሄክታር አረንጓዴ ሥፍራ፣ የሕዝብ መጸዳጃዎች፣ 13 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መጋለቢያ መንገድ፣ 38 የአውቶቡስ እና ታክሲ መጫኛ-ማውረጃዎችን ማካተቱን ገልጸዋል።
እንደዚህ ያሉት ሀገራዊ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሥራዎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን እንደሚያሳድጉ አስረድተዋል።
በተጨማሪም የትራፊክ እንቅስቃሴን በማሻሻል፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን በማጠንከር ደማቅ ለእንቅስቃሴ ምቹ እና ዘላቂነት ያላቸው የከተማ ሥፍራዎች በመፍጠር ረገድ ዐቢይ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።