ሕዝባችንን በታማኝነት፣ በቅንነት ለማገልገል የገባነውን ቃል ቆጥረን እየተገበርን እንገኛለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕዝባችንን በታማኝነት፣ በቅንነት ለማገልገል የገባነውን ቃል ቆጥረን እየተገበርን እንገኛለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከሳርቤት – ጀርመን አደባባይ- ጋርመነት ፉሪ የሚዘልቀው የኮሪደር ልማት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባላት በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
የፕሮጀክቱን መመረቅ አስመልክቶ ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሕዝባችንን በታማኝነት፣ በቅንነት ለማገልገል የገባነውን ቃል ቆጥረን እየተገበርን እንገኛለን ብለዋል።
የተሰሩት መሰረተ ልማቶች ከተማዋን ለኑሮ ምቹ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጋት፣ ሰፊ የስራ ዕድል የፈጠሩ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ መሰረታዊ ለዉጥ ማምጣት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በልማቱ ከመሬት በላይ እና በታች የተሰሩ መሰረታዊ ስራዎች አገልግሎት የሚያሳልጡ፣ ከተማዋን በዘላቂነት ስማርት ሲቲ ለማድረግ የተሰነቀውን ራዕይ ለማሳካት የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ እሴት፤ የስበት ማዕከል የሆኑ ፅዳት፣ ውበት፣ አገልግሎትን ያጣመሩ ስራዎችም በስፋት ተሰርተዋል ብለዋል።
ይህ የኮሪደር ልማት በሁለተኛ ዙር ከጀመርነው 6ኛዉና ከካዛንቺስ ኮሪደር ቀጥሎ በከተማችን ሁለተኛው ረጅሙ እና ሰፋ ያለ አካባቢ የሚሸፍን ሲሆን ከ589 ሄክታር በላይ ቦታ የለማበት ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በዚህም:-
👉 እስከ 60 ሜትር የሚሰፋ 16 ነጥብ 5 ኪ.ሜ አስፓልት መንገድ ( በተጨማሪ 3 ነጥብ 5 ኪ. ሜ የውስጥ ለውስጥ መንገድ) ያለው፣
👉 33 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ፣
👉 13 ነጥብ 3 ኪ.ሜ የሳይክል መንገድ፣
👉 21 የተለያዩ ፕላዛዎች፣
👉 ክረምት ከበጋ፣ በቀን እና በምሽት አገልግሎት የሚሰጡ 20 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣
👉 20 የልጆች መጫወቻ ቦታዎች፣
👉 5 ነጥብ 2 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት፣
👉 20 የመኪና ማቆሚያ ቦታና ተርሚናሎች፣ 1 የመኪና ቻርጂንግ ስቴሽን፣
👉 በግለሰቦች እና በመንግስት የተገነቡ 1 ሺህ 107 የንግድ ቤቶች፣
👉 50 ነጥብ 5 ሄክታር ስፋት ያላቸዉ አረንጓዴ ቦታዎች፣
👉 40 የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣
👉 38 የታክሲና አውቶቡስ ቤይ፣
👉 13 ካፌዎች እና 1 ሬስቶራንት እንዲሁም ከ1 ሄክታር በላይ የነርሰሪ ቦታን በዉስጡ አካትቶ ይዟል።
ይህ ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት፣ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል እና የእውቀት ሽግግር የፈጠረ፣ ለነዋሪዎች ምቾትን ያጎናፀፈ ግዙፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በታለመለት ጊዜ በጥራት እና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል።