የኮይሻ ፕሮጀክትን የማዳን ስራ ተሰርቷል – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክትን የማዳን ስራ ተሰርቷል አሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)።
‘የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምልከታ በኮይሻ’ በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ውይይት በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር አድርገዋል።
አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ያደረጉት ጉዞ ከፍተኛ በረከት አስገኝቷል።
ፕሮጀክቱ ፋይናንስ ከውጪ ተገኝቶለት ይሰራል ተብሎ መጀመሩን አስታውሰው፥ ነገር ግን የቆመ እና ስራ ማስኬድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ የደረሰ ፕሮጀክት ነበር ብለዋል።
በዚህም ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በራሳችን እንደገነባነው ሁሉ ይሄንን ፕሮጀክት በራሳችን እንጨርሰዋለን በሚል በቀጥታ በተሰጠ ውሳኔ እና አመራር እዚህ ደረጃ ደርሷል ነው ያሉት።
ይህ ፕሮጀክት ከኃይል ማመንጫነቱ በተጨማሪ በሚይዘው ውሃ ላይ የመጓጓዣ መንገዶችን የሚፈጥር እንደንሆነ አንስተው፥ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር አመስግነዋል።
በዮናስ ጌትነት